BiT እና FBPIDI የአቅም ግንባታ ቁርኝት ፕሮግራም ተፈራረሙ

የባህር ዳር ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት (BiT) እና የኢትዮጵያ የምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲቲዩካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት (FBPIDI) የቁርኝት ፕሮግራም ስምምነት አደረጉ፡፡ ሁለቱ ተቋማት ቁርኝቱን ያደረጉት FBPIDI በ2010 ዓ.ም. አውጥቶ የነበረውን በምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አቅም ግንባታ ላይ ያተኮረና አምስት ዩኒቨርሲቲዎች የተሳተፉበት ጨረታ BiT አሸናፊ በመሆኑ ነው፡፡ የተቋማቱ ቁርኝት የአጭርና የረጅም ጊዜ (MSc እና PhD) ሥልጠናዎችን፣የሥርዓተ-ትምህርት ክለሳና ዝግጅት ስራዎችን፣ የማማከር አገልግሎት፣ የቤተሙከራ አገልግሎት፣ የቤተሙከራ accreditation እና የምርምር ስራዎችን በዋናነት ያካትታል፡፡  
የባህር ዳር ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰይፉ አድማሱ እና የኬሚካልና ምግብ ምህንድስና ፋኩልቲ ዲን አቶ አሊ ሰይድ እንደገለፁት ከምግብና መጠጥ፤ ከምግብ ጥራትና ደህንነት እና ከአፕላይድ ሂዩማን ኑትሪሽን ቼሮች የተውጣጡ ሰባት መምህራንን ያካተተ ኮሚቴ ተቋቁሞ የቴክኒካልና ፋይናንሽያል ፕሮፖዛሎችን አዘጋጅቶ ለመ/ቤቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ አቅርቦ ነበር፡፡ በዚሁም መሠረት በታህሳስ 2011 ዓ.ም. BiT ጨረታውን ማሸነፉን FBPIDI በደብዳቤ አሳውቋል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም ቁርኝቱን ለማድረግ የሚጠቅሙ የመግባቢያ ሰነድ (MoU) እና የውል ስምምነት ሰነዶች (Documents) በFBPIDI ተዘጋጅተው በሁለቱም ተቋማት በቂ ውይይትና መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ ስምምነቱ ተደርጓል፡፡    
በመጨረሻም የሁለቱ ተቋማት ዳይሬክተሮች አቶ ሰሎሞን ታደለ (FBPIDI)፣ ዶ/ር ሰይፉ አድማሱ (BiT)፣ የኬሚካልና ምግብ ምህንድስና ፋኩልቲ ዲን (አቶ አሊ ሰይድ)፣ በBiT የቁርኝቱ አስተባባሪ (ዶ/ር መስፍን ወጋየሁ)፣ የFBPIDI  ም/ዋና ዳይሬክተር (አቶ በቀለ መኩሪያ)፣ በFBPIDI የቁርኝቱ አስተባባሪ (አቶ ዳኛቸው ወንድሙ) እና ሌሎች የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች እንዲሁም የተለያዩ የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪዎችና ሌሎች ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት ሚያዝያ 17/2011 ዓ.ም. በጁፒተር ሆቴል (አዲስ አበባ) ስለ ቁርኝቱና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎች በተዘጋጀው MoU ላይ ፈርመው የሥምምነቱ ሥነ-ሥርዓት ተዘግቷል፡፡

Share