የአቶ ቢያዝን ሞላ የጡረታ መሸኛ ፕሮግራም

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባህር ዳር ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት የኤሌክትሪካልና ኮምፒዩተር ምህንድስና ፋኩልቲ መምህር ለነበሩት አቶ ቢያዝን ሞላ የጡረታ መሸኛ ፕሮግራም ተካሄደ
-----------------------------------------------
ዛሬ ነሐሴ 18/2013 ዓ.ም. በተካሄደው የአቶ ቢያዝን ሞላ የጡረታ መሸኛ ፕሮግራም ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘና፣ የኢንስቲትዩቱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰይፉ አድማሱን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች፣ጓደኞቻቸውና ወዳጆቻቸው ተገኝተዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰይፉ አድማሱ እንደገለጹት ይህ ፕሮግራም በተቋሙ እንዲዘጋጅ የተወሰነው በርካታ አመታትን በኢንስቲትዩቱ ያገለገሉት አቶ ቢያዝን ሞላ ለተቋሙ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት ሲሆን በተለይም በተመረቁበት የኮምፒዩተር ምህንድስና ሙያ ዘርፍ ለረዥም ጊዜ በማስተማር ብቁ ባለሙያወችን ከማፍራት ባሻገር የኢንስቲትዩቱን የኮምፒዩተር ላቦራቶሪዎች ከማደራጅት እና በአይሲቲና ኔትወርክ አድሚኒስትሬሽን መስክ መጠነ ሰፊ ስራ በመስራታቸውም ጭምር ነው ብለዋል፡፡ በማስከተልም በአቶ ቢያዝን ሞላ ተቋማዊ አበርክቶዎች ዙሪያ የተዘጋጀው ጽሁፍ እንዲነበብ ጋብዘው ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡
በጽሁፉም አቶ ቢያዝን ከውልደታቸው አንስቶ ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ ያለው የህይወት ታሪካቸው የተዳሰሰ ሲሆን በተለይም በባህር ዳር ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት በመምህርነት ተቀጥረው ማገልገል ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ያከናወኗቸው አንኳር አንኳር ተግባራት ተካትተውበታል፡፡ የኮምፒውተር ቴክኖሎጅን በማስተዋዎቅ ረገድም ከኢንስቲትዩቱ አልፈው በባህር ዳር ከተማ ደረጃ ግንባር ቀደም ለመሆናቸው በብዙዎቹ እንደተመሰከረላቸውም ተመላክቷል፡፡
ለተቋማዊ አበርክቷቸው እውቅና ለመስጠት ኢንስቲትዩቱ ያዘጋጀላቸው ስጦታወች በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ አማካኝነት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ከስጦታዎች መካከል አንደኛው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናን የሚገልጽ በቢአይቲ ሜከር ስፔስ ከብርጭቆ የተሰራ ስጦታ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በኤሌክትሪካልና ኮምፒዩተር ምህንድስና ፋኩልቲ ስር የሚገኝ አንድ ላብራቶሪ በስማቸው መሰየሙን የሚግልጽ ስጦታ ነው፡፡ ስያሜው ፋኩልቲው በአካዳሚክ ኮሚሽኑ አማካኝነት ‘Hardware Lab’ በመባል የሚታወቀው ላቦራቶሪ ለፋኩልቲው ከነበራቸው ሚና አንጻር ‘Biazen Molla Hardware Lab’ በመባል እንዲጠራ ወስኖ የማኔጅመንት ካውንስል በማጽደቁ የተሰጠ መጠሪያ ነው፡፡
ዶ/ር ፍሬው ስጦታውን ካበረክቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር የአቶ ቢያዝንን ጡረታ መውጣት አስመልክቶ ይህ ፕሮግራም መዘጋጀቱ እንደ ትልቅ የአስተሳሰብ ለውጥ እንደሚያዩት ገልጸዋል፡፡ ለዚህም እንደምክንያትነት የገለጹት ደግሞ ብዙ ጊዜ የተለመደው ሰው በህይወት ከተለየን በኋላ እንጂ ቆሞ እያለ እውቅና የመስጠት ባህላችን ደካማ መሆኑን ሲሆን እኛ ዛሬ ላይ መምህርና አመራር ለሆንንበት ዩኒቨርሲቲ የአቶ ቢያዝንና ባልደረቦቻቸው አሻራ ለዛሬው ቁመናው ወሳኝ ሚና ተጫውቷል በማለት መስክረውና ለጡረታ በመብቃታቸውም እድለኛ መሆናቸውን ጠቁመው ምንም እንኳ በጡረታ ቢለዩንም በሃሳብ ከዩኒቨርሲቲው ጎን ሆነው እንደሚቀጥሉ በተለይም በስማቸው የተሰየመው ላቦራቶሪ ብዙ ቢያዝኖችን እንዲያፈራ ምክራቸው እንደማይለይ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም አቶ ቢያዝን ለዚህ በመብቃታቸው እንኳን ደስ አለወት በማለትና ረዥም እድሜና ጤናን በመመኘት ንግግራቸውን አብቅተዋል፡፡
አቶ ቢያዝን ሞላ በበኩላቸው በተደረገላቸው ዝግጅትና የተበረከተላቸው ስጦታ መደሰታቸውን ገልጸው ለሁሉም ተሳታፊዎች ያላቸውን አክብሮትና ምስጋናን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ለፕሮግራሙ ተሳታፊዎች የራት ግብዣ መርሃ ግብር የተካሄደ ሲሆን የተዘጋጀውን ኬክም አቶ ቢያዝን ቆርሰዋል፡፡ የዝግጅት ክፍላችንም ለአቶ ቢያዝን ለጡረታ በመብቃታቸው እንኳን ደስ አለዎት እያልን ቀሪ ዘመንዎት የደስታና የመዝናኛ ጊዜ እንዲሆንልዎት እንመኛልን፡፡
images: 
Share