ኢትዮ ክሊክስ ከባሕር ዳር ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት- ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በዛሬው ዕለት በበይነ መረብ በተካሄደ ፕሮግራም አስመረቀ

 
[ህዳር 11/2015 ዓ.ም፣ ባ/ዳር - ኢስኮ/ባቴኢ]
==============================
በኢትዮ ክሊክስ በኩል አቶ ኢዘዲን አሰፋ ከአሜሪካ ፕሮግራሙን ያስጀመሩት ሲሆን ምረቃውን አስመልክቶ ያዘጋጁትን ቪድዮ ለተሳታፊዎች አስመልክተዋል:: በቪድዮ እንደተመላከተው ስልጠናው የተሰጠው በAI and Machine Learning, UI Developement, Cyber Security እና በመሳሰሉት ዘርፎች ሲሆን የሰለጠኑት ተማሪዎችም ባገኙት ክህሎት ተጠቅመው የሰሯቸውን ተግባራት በቪድዮው አመላክተዋል:: እንደ አቶ ኢዘዲን ገለጻ ይህ የመጀመርያ ዙር ስልጠና ሲሆን ተማሪዎቹ መደበኛ ትምህርታቸውን ተመርቀው እስኪወጡ በተለያየ ሂደት የሚቀጥልና መሆኑን ጠቁመዋል:: አስከትለውም ስለ ኢትዩ ክሊክስ ኩባንያ እና አላማዎቹ ለተሳታፊዎች በማብራራት የባሕር ዳር ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ላደረገው አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል::
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጌትነት በበኩላቸው ኢትዮ ክሊክስ ከኢንስቲትዩቱ ጋር የመግባቢያ ሰነድ በተፈራረመ ማግስት ስምምነቱን ወደ ተግባር በመቀየር ተማሪዎችን አሰልጥኖ ለውጤት ማብቃቱ የሚያስመሰግነው እንደሆነ ገልጸው የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሲስተምና ሶፍትዌር ልማት ላይ ከፍተኛ አቅም እንዳለው በማመላከት አለማቀፋዊነት ዋና እሴቱ ከመሆኑ አንፃር በዘርፉ የሚያሰለጥናቸውም ተማሪዎች ብቁና ተወዳዳሪ ሆነው ከሃገር ውስጥ ባለፈ በአለም ገበያ ተፈላጊ እንዲሆኑ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር መሰል ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል::
የኢንስቲትዩቱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ቢምረው ታምራት በበኩላቸው ፕሮግራሙን ላዘጋጁ አካላት ምስጋና አቅርበው ምንም እንኳን ዩኒቨርሲቲዎች በተግባር የተደገፈ መማር ማስተማር ቢያከናውኑም ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን ትምህርት በተጨባጭ የአገራዊና አለማቀፋዊ ኩባንያዎችን ችግር በማምጣት ችግር ፈች ስራዎች እንዲሰሩ መሰል ስልጠናዎች ሚናቸው የጎላ መሆኑን ጠቁመው ስልጠናው በትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ሁሉም አካላት ሃገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል:: በመጨረሻም የመጀመሪያውን ዙር ስልጠና አጠናቀው ለተመረቁ ተማሪዎች አሰልጣኞችና አስተባባሪዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::
 
የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት
ቴሌግራም፡- https://t.me/bitpoly
ዌብሳይት፡- https://bit.bdu.edu.et
 
    
Share