የሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ 60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓልን

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ 60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓልን አስመልክቶ የቀድሞ "ፖሊ እና ፔዳ" ተማሪዎች ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ አካሄደ።
[መጋቢት 03/2015 ዓ.ም፣ ባህር ዳር -ኢስኮ/ባቴኢ]
********************************************************
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት በኢንጂነር ግዛቸው አማካኝነት ከቀረበ በኃላ ዶ/ር ፍሬው ተገኜ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ፤ ከማሕበረሰቡ ጋር እና ከዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር እየሰራ ያለውን እና ወደፊትም ሊሰራ ያቀደውን ስራ በሰፊው አብራርተዋል፡፡
በመቀጠልም ኢ/ር ሸዋፈራው የ1963ዓ.ም የኤሌክትሪካል ቴክኖሎጂ ምሩቅ ሲሆኑ የፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት እና ምሩቃን ለሃገር እድገት ያበረከተቸው አስተዋጽዖች የሚል ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፤ የኢንስቲትዩቱን የምስረታ ሒደትና ከስኬታማ ሰዎች ጥቂቶችን አንስተዋል፡፡ ከእነዚህም ፕሮፌሰር ተስፋየ ቢፍቱ በ1959 ዓ.ም ኢንደስትሪያል ኬሚስትሪ ምሩቅ፤ አቶ ታከለ ተፈሪ በ1960 ዓ.ም የእንጨት ቴክኖሎጂ ምሩቅ፤ ኢ/ር ካሳ ወልደሰንበት በ1961ዓ.ም የኤሌክትሪካል ቴክኖሎጂ ምሩቅ፤ አቶ ስዩም ዋልተንጉስ በ1982 ዓ.ም የኤሌክትሪካል ቴክኖሎጂ ምሩቅ፤ኢ/ር ዳንኤል መብርሃቱ(የዳን ቴክኖክራፍት ባለቤት) በ1965ዓ.ም የኤሌክትሪካል ቴክኖሎጂ ምሩቅ እና ኢ/ር ውብሸት (የዋት ኢንጂነሪንግ ባለቤት) በ1965ዓ.ም የፖሊ ተመሪቂ የሆኑትን አስተዋውቀዋል፡፡ ሌሎችም የኢንስቲትዩቱ ተመራቂዎች የሆኑ በርካታ የድርጅት ባለቤቶች ስለድርጅታቸው እና ስለ ስኬታቸው ሂደት ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ሁሉም ለዚህ ስኬት ያበቃቸው በኢንስቲትዩቱ ቆይታቸው ያገኙት እውቀት እንደሆነ መስክረዋል፡፡
በቀጣይ ለሚኖረው ከፍተኛ ሕብረት የ ‘’PAN” (Poly Alumni Network) ሒደት እንደተሞክሮ የቀረበ ሲሆን ከ ‘’PAN” አባላትም በትምህርቱ እና በቢዝነሱ ዘርፍ ስኬታማ የሆኑ ሰዎች ለታሳታፊው የተዋውቁ ሲሆን እንደ ተቋም እና እንደ ሃገር እያደረጉ ያሉት ከፍተኛ አስተዋጽዖ በአጭሩ ቀርበዋል፡፡ ወደፊትም ዩኒቨርሲቲው ሊሰራ ባሰባቸው የማሕበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክቶችም በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያለውን ስራ ለመደገፍ ቃል ገብተዋል፡፡
በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን እና ስትራቴጂክ ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ ለጉባኤው መሳካት የበኩላቸውን ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ዩኒቨርሲቲው ለሳይንስ ሙያ እድገትና ለሀገር እድገት ልዩ አስተዋፅዖ ላበረከቱ የቀድሞ ተማሪዎች እውቅና እንደሚሰጥም ቃል ገብቷል። ሁሉም የቀድሞ ተመራቂዎች በሰኔ ወር የመጀመሪያ ሳምንት የሚከበረውን 60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል የመዝጊያ ስነስርአት እና የተመራቂዎች ቀንን ወደ ባህር ዳር በመምጣት እንዲያከብሩም ጥሪ አቅርበዋል።
መርሐግብሩም በብሔራዊ አልኮል ፋብሪካ ዘመናዊ አዳራሽ የተካሔደ ሲሆን የመርሐግብሩን አብዛኛው ወጪ በፋብሪካው ስፖንሰር አድራጊነት መሸፈኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት
ቴሌግራም፡- https://t.me/bitpoly
ዌብሳይት፡- https://bit.bdu.edu.et
Share