በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ (GERD) ጉብኝት

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ (GERD) ተገኝቶ የዩኒቨርሲቲውን 60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል አከበረ።
[የካቲት 30/2015 ዓ.ም፣ ባህር ዳር -ኢስኮ/ባቴኢ]
********************************************************
በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ንጉስ ነገስት ዘኢትዮጵያ እና የቀድሞው የሶቪዮት ህብረት መንግስት በ1955 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ የጀመረው የቀድሞው የባህር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት የአሁኑ ባህርዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዮ በዓሉን በGERD አክብሯል። ባከባበሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማኔጅንግ ዳይሬክተር ዶ/ር ምንይችል ግታው፣ 60ኛ ዓመት በዓሉ በዚህ ሁኔታ በሀገራዊ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ማክበር የተሻለ መልዕክት እንደሚያስተላልፍና የፕሮጀክቱንም ሰራተኞች ማበረታታት እንደሚችል ገልጸዋል። ባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መሃንዲሶችን በማፍራት፣ በውሃና ሃይድሮሎጂ ስራዎች ላይ በርካታ ጥናቶችን በማድረግና እንዲሁም የተቋሙ ሰራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለህዳሴ ግድብ በመለገስ ጉልህ ሚና እንደነበራቸውም ገልጸው የበዓሉም ዓላማ ሁሉንም ፈተናዎች ተቋቁሞ ግድቡ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ላስቻሉት ምስጋናና እውቅና ለመስጠት፣ እንደ ቴክኖሎጂ ተቋምም በሁሉም አቅጣጫ ድጋፋቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸው የኢትዮጵያ ህዝብም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ የጀመረውን ርብርብ በተሻለ መልኩ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመቀጠልም አቶ ተመስገን ጌትነት የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር 60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዮ ክብረበዓልን አስመልክቶ በሰጡት ገለጻ፣ የበዓሉ አከባበር የውስጥና የውጪ አካላት የ60ኛ ዓመት ስኬት ጉዞዓችንን እንዲያውቁ ማስቻል፣ ለዚህ ስኬት ያበቁንን ግለሰቦች፣ ማህበረሰብና ተቋማትን ማመስገንና እውቅና መስጠት፣ የተቋሙን ሀገራቀፋዊና አለማቀፋዊ ክሱንነትን መጨመር መሆኑን አብራርቷል። ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ለባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መሰረት የጣሉና ለግድቡም ስራ የመነሻ ሃሳብ ያፈለቁ በመሆናቸው የሳቸውን ስራ ማመስገንና መዘከርም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ የሚለው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መሪ ቃል፣ ዩኒቨርሲቲያችን የተነሳው ዓባይ መሰረቴ ነው በማለት መሆኑንና ይህ ግድብ ዓባይን መሰረት አድርጎ የተሰራ በመሆኑ በሁሉም አቅጣጫ አብረን የምንቆምለት ገፅታችን ስለሆነ 60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዮ ክብረ በዓልን እዚህ የማክበራችን አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል። ለዚህም ዩኒቨርሲቲው በሲቪልና ውሃ ምህንድስና ፋኩልቲና በብሉ ናይል ውሃ ኢንስቲትዩት ምሁራን አማካኝነት ስለ ግድቡና ተፋሰስ ሃገራት ተጠቃሚነት በተመለከተ በየግዜው የምርምር ውጤቶችን እንደሚያበረክት አክለዋል። ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስቀድሞም ለአረንጓዴ አሻራም ትኩረት በመስጠት በተለያዩ ቦታዎች ያደረገውንና እያደረገው ያለውን እንቅስቃሴ ግድቡን ከደለል ተፅኖ ለመከላከልም ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። በመጨረሻም ከ200 በላይ አለም አቀፍ አጋር አካላት ያሉት ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በየመድረኮቹ ስለ ግድቡ ጠቀሜታ በማንሳት እንዲሁም ጎረቤት ሃገራት ድረስ ሄዶ ፕሮግራሞች በመክፈትና የትምህርት እድል በመስጠት የዲፕሎማሲ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነም አስገንዝበዋል::
የታችኞቹ ተፋሰስ አገራቶች ጋር በነበረው ግጭት አፈታት ላይ ተሳትፈው ለግጭት አፈታቱ የመነሻ ቴክኒካዊ ነጥቦች የሰጡት ዶ/ር አሰግደው ጋሻውም ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። እንደ እሳቸው ገለጻም የታችኛው ተፋሰስ አገራት ከፍተኛ ተፅኖ ሲያደርሱት የነበረውና የሚፈሩት ከዚህ በኋላ ዓባይ ላይ ሊሰሩ የታቀዱትን ግድቦችና የመስኖ ስራዎችን ለመስራት ይህ ግድብ አቅም ይፈጥራል በሚል ፍራቻ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ከሌሎች ጠንካራ ተደራዳሪዎች ጋር በመሆን የምላሽ ነጥቦችን ሲያዘጋጁ እንደነበረና በዚህም ረገድ እስካሁን የተሳካ ጉዞ እንደተሄደ ገልጸዋል።
በመቀጥልም ባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የግድቡ አመራሮች በአለፉት አመታት ተጽዕኖዎችን ተቋቁመው በስኬት ስራዎችን እያስኬዱ በመሆናቸው እና ላስመዘገቡት ጉልህ አስተዋፃኦም በSeifu BiT Makerspace የተዘጋጀውን የምስጋና ስጦታዎችን አበርክቷል።
ዶ/ር ቢምረው ታምራት፣ የባህር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንትፊክ ዳይሬክተር በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ሁሌም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጎን እንደሚቆሙ በመግለጽ ለሦስት ሰራተኞችም ነጻ የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት እድል ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
በሌላ በኩል አቶ በላቸው ካሳሁን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምክትል ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው፣ ግድቡ ድረስ በመምጣት ይህንን የመሰለ ማበረታቻና የ60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዮ ክብረ በዓልን ኢንስቲትዩቱ በማክበሩ ለሁሉም ሰራተኞች ትልቅ ተነሳሽነትና የሞራል ስንቅ እንድሚሆነው ተናግረዋል። በመቀጠልም አቶ በላቸው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፍሬ የሆኑት በርካታ ባለሞያዎች በተለያዩ የምህንድስና ስራዎች ተሰማርተው እየሰሩ በመሆናቸው ለዩኒቨርሲቲው ትልቅ ምስጋና አቅርበዋል። የተረከቧቸው ስጦታዎችም ለሁሉም ሰራተኞች አበረታች እንደሆኑ አክለዋል። በዕለቱ 60ኛ ዓመቱን አስመልክቶ የተዘጋጀውን ኬክ የተቋሙ ማኔጅንግ ዳይሬክተር፣ ም/ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ፣ የግድቡ ም/ስራ አስኪያጅ እና በፕሮጀክቱ ተቀጥረው እየሰሩ የሚገኙት የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ተማሪ በጋራ ቆርሰዋል::
በመጨረሻም የባህር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር መኳንንት አገኘሁ በማጠቃለያ ንግግራቸው፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ፣ በተማሪዎች ምርጫና በምርምር ቀዳሚ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን በመቀጠልም ለመላዉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አመራሮችና ሰራተኞች ላደረጉት ትብብር ፣ ለኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት እና የሙያ ማጎልበቻ ማዕከሉ እንዲሁም የቢ አይ ቲ ትሬዲንግ የ60ኛ ዓመት በዓል አከባበርን በማዘጋጀት ላደረጉት ጉልህ ድርሻ ምስጋናን በማቅረብ ንግግራቸውን ቋጭተዋል።
የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት
ቴሌግራም፡- https://t.me/bitpoly
ዌብሳይት፡- https://bit.bdu.edu.et
Share