በባህር ዳር ዩንቨርሲቲ የባህርዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተለያዩ የትምህርት መስኮች ሲማሩ የቆዩ ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት አስመረቀ

በባህር ዳር ዩንቨርሲቲ የባህርዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተለያዩ የትምህርት መስኮች ሲማሩ የቆዩ ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት አስመረቀ
[(July 22, 2023, ISC/BiT-BDU, Bahir Dar)]
***********************************************************************************************************
(ሀምሌ 15/ 2015 ዓ.ም ISC/BiT) በባህርዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 1,015 ሺህ ተማሪዎችን አስመረቀ፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 807 በመጀመሪያ ዲግሪ፣ 203 በሁለተኛ ዲግሪ እና 05 ተማሪዎች በሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በመደበኛው ፕሮግራም ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው። በምረቃ በመርሃ ግብሩ ላይ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፍለ እና ሌሎች የክልል ባለስልጣናት በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፍለ ለተመራቂ ተማሪዎችን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንደተናገሩት ባህርዳር ዩንቨርስቲ ላለፋት ስልሳ አመታት ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለአለም ዕውቀትን ለማስፋት የሚተጉ፣ ልማትን ለማሳደግ የሚሰሩ፣ የሰውን ህይወት ለማሻሻል ብቃት ያላቸው ከፍተኛ የሰው ሀይል በማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አቀርክቷል። አክለውም ዩኒቨርሲቲው በማስተማር፣ በምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት ተልዕኮውን ለመወጣት በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ዕውቀትን እያሰፋ፣ ምርምርን እያጠናከረ፣ ቴክኖሎጂን እያስተዋወቀና ለሀገራችን እያደረገ ያለው ብቃት ያለው የሰው ሃይል ማፍራ የሚደነቅና የሚበረታታ ነው ብለዋል። በመጨረሻም ተመራቂ ተማሪዎች በዩንቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀት፣ ቴክኖሎጂ፣ ተሞክሮ፣ ክህሎትና ስነምግባር ስንቅ አድርገው ሀገርን የሚጠቅም ስራ ይሰሩ ዘንድ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በምረቃ መርሐ-ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት ንግግራቸው የዘንድሮው ምርቃት ዩኒቪርሲቲው 60ኛ አመት የአልማዝ እዮቤል እዩ በዓሉን ባከበረበት አመት መሆኑ ልዩ የሚያደርገው መሆኑን ገልጸዋል። ተያይዞም የባህርዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በቅርቡ የተሰጠውን የብሔራዊ ፈተና 97/100 ያመጣ መሆኑ ትልቅ ኩራት እንደተሰማቸው በገለጹበት ንግግራቸው እንደተናገሩት መልካም ስም ካተረፉ የአፍሪካ ዩኒቨሪሲቲዎች ተርታ ከመሰለፉ ጋር ተያይዞ 60 አመታትን በትጋት እና በጥራት ተምሳሌትነት መቆየቱን አውስተዋል። በመጨረሻም ተመራቂዎች ሃገራችውን በተቻላቸው አቅም ሁሉ በማገልገል ከጠንካራ እና ያደጉ ሃገራት ተርታ እንዲያሰልፉ በመጠየቅ ዩኒቨርሲቲው እዚህ እንዲደርስ ጉልህ ሚና የተጫወቱ አካላትን አመስግነዋል።
የባህርዳር ዩንቨርስቲ የ2015 ዓ.ም የመደበኛ የተማሪዎች ምረቃ ፕሮግራም ላይ ለሁለት ሰዎች የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷል። የመጀመሪዋ የክብር ዶክተሬት ተቀባይ የጠንካራ ጋዜጠኝነት ተምሳሌትና የባለታሪኮች ባለ አደራ ጋዜጠኛ ማዕዛ ብሩ ናቸው። እንዲሁም በግብርና ልማት ዘርፍ በተለይም በሆርቲካልቸር ማለትም በአትክልትና ፍራፍሬ ተያያዠ ስራዎች በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ አስተዋጽኦ ያበረከተው ጌሪት ሆትላንድ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸው።
በስነስርዓቱ ላይ ከየፋኩልቲያቸው የላቀ ውጤት ያመጡ ተመራቂዎች የሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆኑ በአጠቃላይ ከባህርዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተመራቂ ተማሪወች መካከል የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተማሪ የሆነው ዮርዳኖስ ውለታው 3.98 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል። በሌላ በኩል የባለብዙ ክህሎት ባለቤትና የኢንስቲትዩቱ ተመራቂ የሆነው መሰንበት ንጉሴ ግርማዊነታቸው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በቀድሞ አጠራሩ የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩትን በመመስረት ለባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እዚህ መድረስ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ለመዘከር በማሰብ የሳለውን ስዕል ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት በስጦታነት አስረክቧል::
Information and Strategic Communication Directorate
Share