በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባህር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) የፕሮጀክት ዲዛይኖች ላይ የምክክር መድረክ አካሄዱ


ዛሬ ጥቅምት 11/2014 ዓ.ም በባህር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ላይ በነበረው የውይይት መድረክ የባህር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ባንተላይ ስንታየሁ ተቋሙ ሁለት የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን ማለትም የልዩ አዳሪ ት/ቤት ግንባታ ዲዛይን እና የጢስ አባሊማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ፋብሪካ ዲዛይን ከአዋጭነት ጥናት እስከ ሙሉ ዲዛይን በተቋሙ ሰራተኞች አማካኝነት በነፃ ሰርቶ ለአልማ ማቅረቡን ጠቅሰው በተጨማሪም አልማ በራሱ ያሰራቸው በአምስት ከተሞች የሚገነቡ የአልማ የገቢ ማስገኛ ህንጻ ዲዛይን እና የዋንዛዬ ሎጂ ዲዛይን በውይይቱ ላይ እንደሚቀርቡ ጠቅሰው የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘን ውይይቱን እንዲከፍቱ ጋብዘዋል፡፡ የመክፈቻ ንግግር ያድረጉት ዶ/ር ፍሬው የማህበረሰብ አገልግሎት ማለት የፍቃድ አገልግሎት መሆኑን ጠቅሰው በዚህ የማህበረሰብ አገልግሎት ላይ የተሳተፉ የዩኒቨርሲቲውን ማህብረሰብ በማመስገንና ይህ አገልግሎት በርካታ የገንዘብ መጠን ለተጠቃሚው አካል እንደሚያስቀርለት በማውሳት የውይይቱን መርሃ ግብር ከፍተዋል፡፡በመቀጠልም የአልማ ም/ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ መዝገበ አንዷለም በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ ተቋማት ማለትም ከት/ት ቢሮ፣ ከባሕር ዳር ከተማ የተለያዩ ባንኮች ፣ ሥራና ከተማ ቢሮ፣ ባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት፣ ዋሊያ ቲክኖሎጂ፣ አማራ ሕንጻ ስራዎች፣ መንገድ እና ሕንጻ፣ ዲዛይንና ቁጥጥር፣ ላሊበላ አማካሪ፣ የአልማ የባሕር ዳር ኮሚቴ አባላት፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት እና የባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ ፣ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች አካላትም በውይይቱ ላይ የተካተቱ መሆናቸውን በመግለጽ ፕሮጀክቶቹ የሕዝብ ፕሮጀክቶች በመሆናቸው ሁሉም አካል የየራሱን ድርሻ እንዲወስድ እና የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡ በመድረኩ በቀረበው ገለጻ መሰረት ልዩ አዳሪ ት/ቤት ግንባታ በተመረጡ የአማራ ክልል ከተሞች የሚገነቡ ሲሆኑ ከነዚህም መካከል የመጀመሪያው በባሕር ዳር ከተማ በ12 ኪሎ ሜትር ስኩየር ቦታ ላይ የሚያርፍ እስከ 400 የሚደርሱ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸው ከ9-12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን የሚያካትትው ሲሆን ለዚህም ከ210 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ አቶ ቢኒያም በለጠ ተናግረዋል። በመቀጠልም የአልማ ገቢ ማስገኛ ህንጻ ዲዛይን B+G+10 በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገነባ ከ237 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያስፈልግ በአቶ ቢኒያም በለጠ በሌሎች የፕሮጀክቱ አባላት፤ ጢስ አባሊማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ፋብሪካ ዲዛይን በደቡብ ወሎ ከውጫሌ 7 ኪ.ሜ ከ290 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያስፈልግ በዶ/ር በረከት ኃይሌ እና በሌሎች የፕሮጀክቱ አባላት እና በመጨረሻም የዋንዛዬ ሎጂ ዲዛይን በአቶ ኃይሌ የቀረቡ ሲሆን አጠቃላይ የወጪ ትንተና እና የዲዛይን ዝርዝሮች ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡ ሁሉም ፕሮጀክቶች የዲዛይን ገለጻ ከተደረገባችው በኋላ ከታዳሚዎች ከዲዛይን ፤ ከዋጋ ትንተና፤ ለአካባቢው ማህበረሰብ ከሚሰጡት ጥቅም፤ አዳዲስ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት (ዳታ ሴንተር) አብሮ ዲዛይን ጋር ከማካተት፤ ቆሻሻ አውጋገድ እና ሌሎችም በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው በዲዛይኑ ባለቤቶች ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ የአማራ ክልል ት/ት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ማተቤ ታፈረ በበኩላቸው በክልሉ ወስጥ ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች እንደሚገኙ ጠቅሰው ልዩ የአዳሪ ት/ት ቤት ከመገንባት አንጻር ክልሉ ወደ ኋላ እንደቀረ በመጥቀስ ወደፊት በሌሎች ከተሞችም ተጨማሪ የአዳሪ ት/ት ቤቶች እንዲገነቡ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም የባህር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳ/ዳይሬክተር ዶ/ር ሰይፉ አድማሱ ሁሉንም የውይይቱ ተሳታፊዎች አመስግነው የዲዛይን ስራው ላይ የተሳተፉትን ሰዎች የሰራችሁት ለአማራ ህዝብ ነው፤ በማለት ከላይ የተሰጡትን አስተያየቶች በመጨመር ወደፊት እነዚህ ዲዛይኖች በጥልቀት እንዲገመገሙ ተቋሙ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ በመግለጽ ለአማራ ልማት ማህበር ተጨማሪ ስራዎችን ለመስራት ዝግጁ ነን፤ ጠይቁን እናገለግላለን በማለት የውይይት መርሃ ግብሩን ዘግተዋል፡
 

Share