ክፍት የኃላፊነት ቦታ ማስታወቂያ

Body: 

                                                                                                                                                                                            ቀን፡06/08/2014 ዓ.ም

ክፍት የኃላፊነት ቦታ ማስታወቂያ

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕር ዳር ቴክኖሎጅ እና የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ተቋማትን አመራሮች እና አስተዳዳሪዎች ለመምረጥና ለመሰየም ለመደንገግ ነሃሴ/2013ዓ.ም የወጣውን መመሪያ ቁጥር 01/2021 መሰረት በማድረግ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለባሕር ዳር ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት የሳይንቲፊክ ዳይሬክተር የኃላፊነት ቦታ ላይ ለአራት አመታት ማገልገል የሚችሉ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ  አመልካቾችን አወዳድሮ ለመመደብ ይፈልጋል፡፡

የመወዳደሪያ መስፈርት፡-

1ኛ. የትምህርት ማዕረግ፣ በምህንድስና፣ በቴክኖሎጅ ወይም በሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ረዳት ፕሮፌሰር እና ከዚያ በላይ የሆነ/የሆነች፣

2ኛ. የስራና አመራር ልምድ፡-

ሀ/ በማስተማርና በምርምር ከመጀመሪያ ዲግሪ በኋላ 6 ዓመትና ከዚያ በላይ ልምድ ያለው/ያላት፣

ለ/  ሶስተኛ ዲግሪ ያለዉ/ያላት እና በአመራርነት 2 ዓመት እና ከዚያ በላይ ያገለገለ/ያገለገለች ወይም ሁለተኛ ዲግሪ ያለዉ/ያላት እና በአመራርነት 5 አመት እና ከዚያ በላይ ያገለገለ/ያገለገለች፣

ለስራ መደቡ አግባብነት ያለው የአመራርነት ልምድ ውጤት/ክብደት የሚሰጠው ለእያንዳንዱ  የአገልግሎት ዘመን ሆኖ ለከፍተኛ ደረጃ የኃላፊነት ቦታ 1 ነጥብ፣ ለመካከለኛ ሀላፊነት ቦታ 0.75፣ ለዝቅተኛ ደረጃ የሀላፊነት ቦታ 0.5 ነጥብ ነው፡፡ በኢንዱስትሪው እና አለም አቀፍ ተቋሞች ተሳትፎ የሚገኝ የስራ ልምድ በአገልግሎት ዘመን ላይ የተመሰረተ ሆኖ በማስተማርና ምርምር፣ አገልግሎት ከሚገኘው ልምድ ጋር እኩል ነው፡፡ በማስተማርና ምርምር፣ በኢንዱስትሪ ተሳትፎ እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የስራ ልምዶች  አንድ ላይ ሊደመሩ ይችላሉ፡፡

ማሳሰቢያ፡ ሁሉም ማስረጃዎች ከመስሪያ ቤታቸዉ የሰዉ ሃይል አስተዳድር የተረጋገጠ መሆን አለበት

3ኛ. በማስታወቂያ የተገለጸውን የኃላፊነት ቦታ ተጨባጭ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የከፍተኛ ትምህርትን ተደራሽነት፣ ፍትሀዊነት፣ ጥራትን ተገቢነትና አለም አቀፋዊነት ለማሳካት፣ ተቋሙን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ ተጨማሪ ሀብት ለማስገኘት፣ እንዲሁም አለም አቀፋዊነትና አገራዊ ግንኙነቶችን ለመፍጠርና ለማስፋፋት በሚደረገው ሂደት አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚያስችል ስልታዊ እቅድ (Strategic Plan) ማዘጋጀትና ማብራሪያ መስጠት የሚችል/የምትችል፣

4ኛ. የተቋሙ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ ለዕጩ አፈላላጊና አስመራጭ ኮሚቴ፣ የሴኔት አባላትና ሌሎች የሚመለከታቸው ተጋብዘው በሚገኙበት መድረክ በአጀንዳዎች ላይ በአካል ተገኝቶ/ታ ማብራሪያና ገለፃ መስጠት የሚችል/የምትችል፡፡

5ኛ. ሴት አመልካቾች ይበረታታሉ፡፡

6ኛ. አመልካቾች ከተቋሙ ከማንኛዉም አይነት ፈቃድ (ዕረፍት፣ የትምህርት፣ የምርምር፣ … ወዘተ) ውጭ መሆን አለባቸዉ፡፡

7ኛ. መመዘኛዎች የተሰጣቸው ክብደት

7.1. የትምህርት ደረጃ (25 በመቶ)

7.2. የሥራ እና አመራር ልምድ (25 በመቶ)

7.3. በተወዳዳሪዉ በሚቀርብ አጭር ስልታዊ እቅድ (Strategic Plan) በዕጩ አፈላላጊና አስመራጭ ኮሚቴ የሚሰጥ (20 በመቶ)

7.4. በተወዳዳሪዉ በሚቀርብ አጭር ስልታዊ እቅድ (Strategic Plan) በተቋሙ ማህበረሰብ የሚሰጥ (15 በመቶ)

7.5. በተወዳዳሪዉ በሚቀርብ አጭር ስልታዊ እቅድ (Strategic Plan) በሴኔት አባላት የሚሰጥ (15 በመቶ)

8ኛ. አመልካቾች ለማመልከት ሊያሟሏቸዉ የሚገባ አስፈላጊ ሰነዶች

8.1. ማመልከቻ ደብዳቤ፣

8.2. የግለ ታሪክ መግለጫ (ካሪኩልም ቪቴ)፣

8.3. የትምህርት ማስረጃ ኮፒ፣

8.4. የስራና የአመራር ልምድ፣

8.5. ስልታዊ እቅድ (Strategic Plan) (ከአምስት ገጽ ያልበለጠ)

አመልካቾች ይህ ማስታወቂያ ከወጣበት ከ06/08/2014 ዓ.ም ጀምሮ ለ10 ተከታታይ የስራ ቀናት የትምህርትና የስራ ልምዳቸውን ማስረጃ ፎቶ ኮፒ እንዲሁም ያዘጋጁትን ከ 05 ገጽ ያልበለጠ የሥራ ስልታዊ እቅድ (Strategic Plan) ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ድረስ ማስገባት ይኖርባቸዋል፡፡ አካል ጉዳተኛ አመልካቾች ከሚመለከተዉ አካል ማስረጃ ማቅረብ አለባቸዉ፡፡

ለበለጠ መረጃ በሚከተሉት ስልክ ቁጥሮች በ0932808002/0904951414 ደውለው ማነጋገር ወይም የተቋሙን ድረ-ገጽ bdu.edu.et እና bit.bdu.edu.et መመልከት ይችላሉ፡፡

 

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕር ዳር ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዕጩ አፈላላጊና አስመራጭ ኮሚቴ

Date: 
Thursday, April 14, 2022 - 11