ኢንስቲትዩቶቹ የግንባታ መረጃ ሞዴሊንግ (BIM) ስልጠናን አስጀመሩ

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕርዳር ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በጋራ በመሆን ከዛሬ ጀምሮ ለ20 ቀናት ይቆያል የተባለለትን በግንባታ መረጃ ሞዴሊንግ (Building Information Modeling) ዙሪያ ያተኮረ ስልጠና በቢያዝን ሞላ ሃርድዌር ላቦራቶሪ አስጀምረዋል፡፡ ስልጠናው ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ተሳታፊዎችን ያካተተ ሲሆን የስነ ህንጻ፣ ስነ መዋቅር፣ ፕሮጀክት ማኔጅመንት እና ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች የተካተቱበት እንደሆነ ከመድረኩ ተገልጿል፡፡
የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ም/ዋ/ዳይሬክተር ኢንጂነር ዳዊት መሃሪ ኢንስቲትዩቱ ከ11 መሰል ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራርሞ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው BIMን ለበርካታ አመታት ሲተገብር የቆየ ሲሆን በሃገሪቱ ከ120 በላይ ለሚደርሱ ባለሙያዎችም ስልጠና መስጠቱን አዉስተዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ሃገር በኮንስትራክሽን ዘርፉ ካለብን ችግር አኳያ በቂ ስላልሆነና ኢንስቲትዩቱም ብቻውን ማዳረስ ስለማይችል ዩኒቨርሲቲዎችን ማሳተፍ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት በሰፊው እየተሰራ መሆኑን ለተሳታፊዎች አስገንዝበዋል፡፡ ቴክኖሎጂው ፕሮጀክቶችን በተመደበላቸው ጊዜ፣ ፋይናንስና ጥራት መሰረት ለመጨረስ ወሳኝ ሚና እንዳለው በመንግስት ደረጃም ስለታመነበት ኢንስቲትዩቱ በተለይም ከEthiopian BIM Society ጋር በመተባበር የ10 አመት መሪ ዕቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኢንጅነር ዳዊት በመጨረሻም በዘርፉ ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ አውስተው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይህንን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በካሪኩለም አካትተው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕርዳር ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት አካዳሚክ ም/ሳ/ዳይሬክተር ዶ/ር ደምሰው አልማው በበኩላቸው የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩቱ ተነሳሽነቱን ወስዶ ከትምህርት ተቋማት ጋር ለመስራት ማሰቡና መሰል ስልጠናዎችን ማካሂዱ እንደሚያስመሰግነው ገልጸው ሰልጣኞችም የተመቻቸላቸዉን ስልጠና በትኩረትና በተገቢው መንገድ ሰልጥነው በአለምአቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው ሰርቲፊኬት ባለቤት ከመሆን ባሻገር ሌሎችን አሰልጥነው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ችግር ከመቅረፍ አኳያ ግንባር ቀደም ሚና ሊጫዎቱ አንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። የባሕር ዳር ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩትም በስትራቴጂክ እቅዱ አካትቶ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች ውስጥ አጫጭር ስልጠናዎችን መስጠት ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመው BIM ከነዚህ መስኮች መካከል እንዲሆን ፍላጎት መኖሩን ገልጸው የስልጠናውን በይፋ መጀመር አብስረዋል።
ከኮንስትራክሽን ማነጅመንት ኢንስቲትዩት የመጡት ኢንጅነር ፈለቀ አሰፋም የመጀመርያ ሞጁሎችንና የሚወስዱትን ጊዜ አስተዋውቀው ስልጠናውን መስጠት ጀምረዋል።
ቴሌግራም፡- https://t.me/bitpoly
ዌብሳይት፡- https://bit.bdu.edu.et
Share