የኢንስቲትዩቱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰይፉ አድማሱ ከተለያዩ ከተሞች ለመጡ የባለድርሻ ተቋማት ተወካዮች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ፕሮግራሙን ያስጀመሩት ሲሆን መተግበሪያውን አልምተው ለተለያዩ ከተሞች የውሃ አገልግሎት ተቋማት ሰርተው ላስረከቡት የኢንስቲትዩቱ ባልደረቦች አድናቆታቸውን ችረዋል፡፡ አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታይዝ በማድረግ ቀልጣፋና ዘመናዊ ማድረግ የመንግስት ዋንኛ አቅጣጫ መሆኑን አመላክተው ዩኒቨርሲቲውም ይህንን መሰረት በማድረግ ለዘርፉ ለዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ለተሳታፊዎች አስገንዝበዋል፡፡ አክለውም የለሙት መተግበሪያዎች ለተጠቃሚው ማሕበረሰብና ለተቋማቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸው አውስተው የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር መጠናከር ለመሰል ስኬቶች ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ ሶፍትዌሩን በመስራት የተሳተፉት እና የሲቪል እና ውሀ ሐብት ምህንድስና ፋኩልቲ መምህር የሆኑት አቶ እሸቱ አሰፋ በዕለቱ በመገኘት ስለ ሶፍትዌሩ እነደ መነሻ ይሆን ዘንድ ስለመተግበሪያው አጀማመር፣ አሁን የደረሰበት ሂደት፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ መፍትሄዎች እንዲሁም በቀጣይነት ቡድኑ ስለሚሄድባቸው አቅጣጫዎች ያብራሩ ሲሆን ዛሬ ከተረከቡት 6 ተቋማት በተጨማሪ የባሕር ዳር ከተማን ጨምሮ ሌሎች 5 ከተሞች መተግበሪያውን በማልማት ላይ እንደሆኑና በቅርብ ጊዚያት ውስጥ ተጠናቅቀው ለየተቋማቱ እንደሚረከቡ ገልጸዋል፡፡ ስለ ሶፍትዌሩ ባህሪያት እና በውስጡ ስለሚገኙ ግልጋሎቶች ያብራሩት ደግሞ የኮምፒውቲንግ ፋኩልቲ መምህር የሆኑት አቶ ሙሉጌታ ሙጬ ናቸው።
በርክክቡ ወቅት የኢንስቲትዩቱ UIL እና የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ባንተላይ ስንታየሁ ዘመናዊነቱንና አዋጪ መሆኑን አንስተው በመሃከል ያለውን ሰንሰለት በመበጠስ ከባንክ ቀጥተኛ ግንኙነት መፍጠር እንድሚያስፈልግ ገልጸዋል። የአገልገሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑ ስድስቱም ከተሞች እንጂባራ፣ ዳንግላ፣ ቻግኒ፣ አዲስቅዳም፣ ፈንድቃ እና አዴት የመጡ ባለሙያዎች በበኩላቸው መተግበሪያው ለስራቸው መቅለል ያደርገውን አስተዋጽኦ በመገልጽ ቢስተካከሉ ወይም ቢጨመሩ ያሏቸውን የመተግበሪያው ባህሪያትን አንስተዋል፡፡
እንደማጠቃለያ የኢንስቲትዩቱ ምርምር እና ማሕበረሰብ አገልግሎት ምክትል ሳይቲፊክ ዳይሬክት ዶ/ር መኳንንት አገኘሁ ሶፍትዌር በእርከን የሚሰራ መሆኑን በመጠቆም ሁሉንም ችግሮች በአንዴ ለመፍታት ይቻላል ብሎ መጠበቅ እንደማይገባ ይልቁንም በስራ ወቅት በመፈተሽ እየበለጸገ የሚሄድ መሆኑን አመላክተዋል። በመጨረሻም ከርክክብ በኋላ ወሳኝ ጉዳዩችን ካልሆነ በቀር በሂደት ኢንስቲትዩቱ ከሥርዓቱ እየራቀ ስለሚሄድ ውሃ አገልግሎት ሙሉ ባለቤትነቱን መውሰድ እንድሚጀምር በመግለጽ ውይይቱ ተጠናቋል።
የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት
ቴሌግራም፡- https://t.me/bitpoly
ዌብሳይት፡- https://bit.bdu.edu.et






