ለቀድሞው ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰይፉ አድማሱ የምስጋና ፕሮግራም ተካሄደ

ቤተሰባቸውን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ የኢንስቲትዩቱ አዲሱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር፣ ም/ሳ/ዳይሬክተሮች፣ ዲኖችና ዳይሬክተሮች በተገኙበት ለዶ/ር ሰይፉ አድማሱ የሽኝትና የምስጋና ፕሮግራም ተካሄደ፡፡
ፕሮግራሙ ስለ ዶ/ር ሰይፉ የተደረጉ ምስክርነቶች በቪድዮና በጽሁፍ የቀረቡበት ሲሆን በስራ ጉዳይ ከሃገር ውጭ የሚገኙት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘም በበይነ መረብ በነበራቸው ቃለ ምልልስ  ‘’ ሰይፉ የምርምር፣ የእውቀት፣ የስራ ሰው ነው” ሲሉ የተደመጡ ሲሆን ‘’ማንም ጋር መግባባት የሚችል፣ ባለ ራዕይ፣ ተልዕኮ ተኮር፣ በቡድን ለመስራት የሚመች ቅን ሰው’’ በማለትም አክለዋል፡፡ ፕሬዝደንቱን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ምስጋናቸውንና መልካም ምኞታቸውን የገለጹ ሲሆን ባለቤታቸው ወ/ሮ ኢሌኒና ልጆቻቸውም በተመሳሳይ መልኩ በቪድዮ የተቀረጸው መልዕክታቸው ተላልፏል፡፡
በመቀጠልም የእውቅናና ሽልማት አሰጣጥ መርሃግብር የተካሄደ ሲሆን በተቋሙ የተዘጋጁትን ስጦታዎች በዩኒቨርሲቲው ም/ፕሬዝደንቶች አማካኝነት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ከስጦታዎች መካከል በቀድሞ አጠራሩ BiT Maker Space የሚባለውን Seifu BiT Maker Space በሚል እንዲተካ የኢንስቲትዩቱ ሰኔት ማንዴት መወሰኑን ተከትሎ የተዘጋጀው የማይካ ላይ ህትመት ይገኝበታል፡፡ ሰኔቱ ይህንን ውሳኔ ሲያስተላልፍ በዋናነት ዶ/ር ሰይፉ ለማዕከሉ ያበረከቱትን ጉልህ አስተዋጽኦ መሰረት አድርጎ ሲሆን በም/ፕሬዝደንት ደረጃ አመራር ሆነው ሳለ የስራ ጫናን ተቋቁመው ከዩኒቨርሲቲው ግንባር ቀደም ተመራማሪ ሳይንቲስቶች ውስጥ መመደባቸውም የተለየ ሰለሚያደርጋቸው ጭምር ነው በሚል ከመድረኩ ተገልጿል፡፡ 
በመጨረሻም የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር እሰይ ከበደ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ዝግጅቱን ላስተባበረው የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በመዝጊያ ንግግራቸው እንደገለጹት ዶ/ር ሰይፉ ዛሬ የተደረገላቸው እውቅና ለእሳቸው እዳ ሲሆን በሄዱበት ሁሉ ለማዕከሉ እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው ጠንክረው በመስራት እዳቸውን እንደሚከፍሉ ያላቸውን ዕምነት ጠቁመዋል፡፡  
የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት
ቴሌግራም፡- https://t.me/bitpoly
ዌብሳይት፡- https://bit.bdu.edu.et
Share