በባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኬሚካል እና ምግብ ምሕንድስና ፋኩልቲ ያዘጋጀው ዓመታዊ ወርክሾፕ ተካሄደ

[ሐምሌ 16/2014 ዓ.ም፣ ባሕር ዳር - ኢስኮ/ባቴኢ]
=========================
በወርክሾፑ መግቢያ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ቢምረው ታምራት እንደገለጹት የዩኒቨርሲቲ እና ኢንዱስትሪ ትስስር ወሳኝ ከመሆኑ ባለፈ ተማሪዎችን ብቁ ኢንተርንሺፕ ቆይታ እንዲኖራቸው ያደርጋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመት ቢሮ ሃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው  ያደጉት ሐገራት ደሀ የሚባሉት ሀገራትን ሐብት ለመቀራመት ጥረት እንደሚያደርጉ ጥቁመው የክልሉ መንግስት የኢንዱስትሪ መንደሮችን ገንብቶ ለባለሐብቶች ከመስጠት ባለፈ ብድር በማመቻቸት ኢንዱስትሪው ኢንዲሻሻል ጥረት ያደርጋል። በዚህም የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ማድረግ እና የውጪ ምንዛሬ አቅምን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። 
በሌላ በኩል የዩኒቨርሲቲው አልሙናይ ኢንጅነር ግዛቸው ሽፈራው የኬሚካል እና የምግብ ኢንዱስትሪዎች ሀገር ከመቀየር ባለፈ ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት እንደሚሆኑ ጠቅሰው ኢንዱስትሪዎች እና ዩኒቨርሲቲዎች በተለያየ መንገድ ውስጥ እየተጓዙ በመሆናቸው ማደግ አዳጋች መሆኑን ገልጸዋል። ይህንን በማስመልከት የፋኩልቲው ዲን ዶ/ር መታደል ካሳሁን የፋኩልቲውን አቅም ብሎም በውስጡ የተሰሩ ሥራዎችን ገልፀው ምርምሮችን እና የተማሪዎችን ዓቅም ማጎልበት ላይ እንደሚሰራ ተናግረዋል። በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አድጀንት ፕሮፈሰር ለሊሳ ዳባ የሕዝብ ቁጥር መጨመር አሳሳቢ እንደመሆኑ መጠን እና የወደፊቱ ሕዝብ በብዙ መጨመር በምግብ ራስን የመቻል ስራዎች ላይ አደጋ ደቅኗል። በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ እንደነበረ ገልፀው የኮቪድ መምጣት ኢትዮጵያን ጨምሮ ዓለምን ወደኋላ የጎተተ እንደሆነ ገልፀዋል።
በኢንዱስትሪ ሚንስቴር የኬሚካል እና ኮንስትራክሽን እቃዎች ጥናት ክትትል እና ድጋፍ ዳይሬክተር ወ/ሮ ነጻነት አበበ እንደተናገሩት የሚሰሩበት ክፍል በ70ቹ የነበረው ጥንካሬ ከጥቂት ለውጦች በዘለለ የሚጠበቀውን ያህል አለማደጉ አሳሳቢ እንደሆነ ሁሉ ኢንዱስትሪዎች እንዲያድጉ ሰላም እና የተሳለጠ ቢሮክራሲ የሚያስፈልግ ሆኖ በተናጠል ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ይልቅ መንግስት በሕብረት ለሚከናውኑ ሥራዎች ትኩረት እና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል። ይህም ሚንስቴሩ ደሴት  ሆኖ የሚተገብረው ሳይሆን ከኢዱስትሪዎች እና ትምሕርት ተቋማት ጋር መተባበር መሆኑን ገልፀዋል። በትምሕርት ሚንስቴር የከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት ስልጠና ምርምር እና ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ዳንኤል በበኩላቸው ኢንዱስትሪዎች የሚያመርቷቸውን ምርቶች ጥራት እና ብዛት ከማሳደግ አንጻር እዚህ ግባ ይሚባል ምርምር ካለመሰራቱ ባለፈ ከትምሕርት ተቋማት ጋር ያላቸው ትስስር ደካማ መሆኑ አሳሳቢ መሆኑን ገልፀው ገንዘብ እና የአቅም ውስንነት አስቸጋሪ በሆኑበት ሁኔታ ውስጥ የኢንዱስትሪው ውድድር መድረክ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራስን መቻል አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። 
በእለቱ የተለያዩ ሓሳቦች የተሰነዘሩ እና ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን ሁሉም የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ስምምነት ተደርሷል። በመዝጊያው ወቅት የኢንስቲትዩቱ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር መኳንንት አገኘሁ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ምርምር እና እድገት የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ጠቁመው ኢንስቲትዩቱ ያለውን እምቅ ኃይል እና አቅም ከኢንዱስትሪዎች ጋር ለመስራት የሚያስችለው መሆኑን በመግለጽ በጋራ ሆኖ በትንሹ በመጀመር ወደላቅ ደረጃ መምጣት እንድሚቻል ጠቁመዋል። 
Information and Strategic Communication Directorate
Share