በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የ2014 ዓ.ም የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ አካሄደ

[ሐምሌ 20/2014 ዓ.ም፣ ባሕር ዳር - ኢስኮ/ባቴኢ]
=========================
ኢንስቲትዩቱ ለ3 ተከታታይ ቀናት በጎንደር ከተማ ሲያካሂደው የነበረውን የሪፖርት ግምገማ መድረክ በትናንትናው ዕለት አጠናቅቋል፡፡ በመድረኩ ሁሉም ዲኖች፣ ዳይሬክተሮችና የማስተባበሪያ ቢሮ ሃላፊዎች የየክፍላቸውን አመታዊ የእቅድ ክንውን ሪፖርት በየተራ ያቀረቡ ሲሆን በክንውኖቹ ላይም አስተያየትና ጥያቄዎች ቀርቦባቸው ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ በመጨረሻም የተቋሙ የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በእቅድና በጀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ረዴ በዛብህ አማካኝነት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ 
በመድረኩ የመክፈቻና የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ቢምረው ታምራት ያሳለፍነው የበጀት አመት እንደሃገርም እንደተቋምም ብዙ ፈተናወችና ውጣውረዶች የበዙበት ቢሆንም ሁሉም ክፍሎች ችግሮችን ተቋቁመው እቅዳቸውን ለማሳካት የሄዱበት ርቀት ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ ገልጸው ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ አክለውም የዚህ መድረክ ዋነኛ አላማ በክንውኑ የነበሩ ክፍተቶችን በጋራ የመለየትና ለቀጣይ የበጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ትምህርት ወስዶ ስኬታማ ክንውን ለመፈጸም ወሳኝ ግብዓት ማግኘት እንደነበር ጠቁመው ከዚህ አኳያም መድረኩ ግቡን ያሳካ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
የውይይት መድረኮችን የአ/ም/ሳ/ዳይሬክተሩ ዶ/ር ደምሰው አልማው እና የም/ማ/አ/ም/ሳ/ዳይሬክተሩ ዶ/ር መኳንንት አገኘሁ እየተፈራረቁ የመሩ ሲሆን አጠቃላይ ፕሮግራሙን የተቋሙ ጠቅላላ የጥራት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት አስተባብሯል፡፡ 
Information and Strategic Communication Directorate
 
Share