የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማኅበርን ለማጠናከር እንደሚሠራ አስታወቀ

17 Dec, 2025

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመገኘት ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጋር ውይይት አድርገዋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ በቅርቡ አዲስ ስራ አስፈጻሚ በማቋቋም የዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዶ/ር ደመላሽ መንግሥቱ ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱም ዶ/ር መንገሻ የዩኒቨርሲቲ መምህራን የራሳቸው ማኅበር ስራ አስፈጻሚ በአዲስ መልክ መደራጀቱን በማድነቅ፤ ማኅበሩ ለሀገርና ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚጠበቅበትን ጠቃሚ ሚና እንዲወጣ እንዲሁም ማኅበሩ ይበልጥ ሊጠናከር ስለሚገባባቸው ሁኔታዎች መክረዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዲያቆን ውቤ እንግዳው በበኩላቸው፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአገር አቀፉ ማኅበር ውስጥ የዋና ጸሐፊነት ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር መንገሻ አየነ ማኅበሩ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚያስተምሩና የሚመራመሩ መምህራንን፣ ተመራማሪዎችንና ፕሮፌሰሮችን በአባልነት ያቀፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች የላቀ ሙያዊ አበርክቶ ለማድረግ አቅዶ መሥራት እንዳለበት መክረዋል። አክለውም የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማኅበር (ኢዩመማ) ለሀገር ዕድገት፣ ለዩኒቨርሲቲዎች ራስ-ገዝ (Autonomy) እንቅስቃሴና ለመምህራን ሁለንተናዊ ሕይወት መሻሻል ትልቅ ፋይዳ ያለው ተቋም በመሆኑ በጥንካሬ ሊመራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማኅበሩ አገራዊ ተልዕኮውን እንዲወጣ፣ የዩኒቨርሲቲዎችን ክብርና ድርሻ በማስጠበቅ ረገድ የአስተባባሪነት ሚናውን እንዲያጠናክር አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግና አብሮ ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል።
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደመላሽ መንግሥቱ በቆይታቸው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን የሥራ እንቅስቃሴና የግቢዎቹን ወቅታዊ ሁኔታ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።