በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባህር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (BiT) የህፃናት ማቆያ ማዕከል የአንድ ዓመት የምስረታ እና የምረቃ በዓል ተከበረ

ማዕከሉ የተመሰረተበትን የአንድኛ ዓመት በዓልና የምረቃ ስነ-ስርዓት ምክንያት በማድረግ የመግቢያ ንግግር ያደረጉት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኝ ማዕከሉ እውቅናና ትኩረት ሊሰጡትና ሊያሳድጉት የሚገባ መሆኑን ገልፀው የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ከማገልገል አልፎ ለሌሎች ተቋማትና ድርጅቶችም እንደ አርአያ ሊወሰድ የሚችልበትን ደረጃ መፍጠር እንዳለበት አሳሰበዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አክለውም ዩኒቨርሲቲው ያሉትን የዘርፉ ምሁራን በማካተት ማዕከሉ ሊታገዝ ከቻለ ከሌሎች መሰል መዕከሎች ላቅ ባለ ደረጃ አገልግሎት መስጠት የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚቻልም ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም የህፃናት ማቆያው ለሴት ሠራተኞች ምቹ የስራ ሁኔታን ከመፍጠር አንፃር ብቻ ሳይሆን እናት ሠራተኞቻችን ያለባቸውን የስራ ጫና በመቀነስ ከወንድ እኩል ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል፡፡

የባሀር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰይፉ አድማሱ በበኩላቸው በማዕከሉ ምስረታና አገልግሎት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጽው ማዕከሉ አሁን ያለበትን ደረጃ ለማድረስ ዕገዛ የሰጡ የቀድሞና የአሁን አመራሮችን አመስገነዋል፡፡

የህፃናት ማቆያው በአሁኑ ሰዓት በሦስት ደረጃዎች ተከፍሎ ከ6ወር እስከ 3ዓመት ከ6ወር ላሉ 70 ህፃናት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ያወሱት የተቋሙ አስተባባሪ ወ/ሮ መስከረም ፀሐይ አክለውም ጥያቄ ያቀረቡ የተቋሙ እናት ሠራተኞች በሙሉ መስተናገዳቸውን ገልፀዋል፡፡

መዕከሉ በአሁኑ ሰዓት ዘጠኝ የህፃናት ሞግዚቶች፣ አንድ የሞግዚቶች ተቆጣጣሪ ፣አራት የጽዳት ሠራተኞች እና አንድ አትክልተኛ ሲኖሩት ባጠቃላይ ለ15 ግለሰቦች የስራ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ አሁን ያለበት የጥራት ደረጃና የተሻለ አገልግሎት እንዳለ ሆኖ ተጨማሪ ድጋፍና እገዛ እንደሚያስፈልገው የፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት  ረ/ፕሮፌሰር ሲስተር ኤደን አምሳሉ ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም፣ ዝግጅቱ ለማዕከሉ መመስረት አብይ አስተዋፅኦ ለነበራቸው ግልሰቦች፣ የስራ ክፍሎች እና የህጻናት ተንከባካቢዎች የምስጋና የምስክር ወረቀት በመስጠት ተጠናቋል፡፡ 

images: 
Share