በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን ጨምሮ የ3 ዩኒቨርሲቲ የሥራ ፈጠራ ጀማሪ ተማሪዎችን ማዕከል ያደረገው አውደ ርዕይ

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን ጨምሮ የ3 ዩኒቨርሲቲ የሥራ ፈጠራ ጀማሪ ተማሪዎችን ማዕከል ያደረገው አውደ ርዕይ ተጠናቀቀ።
[መጋቢት 03/2015 ዓ.ም፣ ባህር ዳር -ኢስኮ/ባቴኢ]
********************************************************
ለ7 ተከታታይ ቀናት በBiTec BiT-BDU “Design your Venture (DYV) Workshop for University Student Startups” በሚል ርዕስ ከባሕር ዳር፣ ሐዋሳ እና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለተመረጡ ተማሪዎች ከMInT, MoE፣ EDI እና UNDP ጋር በመተባበር ሲሰጠ የነበረው ስልጠና ዛሬ ፍጻሜውን ያገኘ ሲሆን በመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ የዩኒቨርሲቲውን 60 ዓመታት የስኬት ጉዞ አብራርተዋል። በንግግራቸውም ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር አብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከሠልጣኞቹ ውስጥ የሶስቱም ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ተማሪዎች ከሥልጠናው ያገኙትን ጥቅም አንስተው ያብራሩ ሲሆን ድጋፍ ያድረጉላቸውን አካላት በሙሉ አመሥግነው በቀጣይ ለመሥራት ላሰቡት የፈጠራ ሥራ ትልቅ መሰረት እንደሆናቸውም ተናግረዋል። የ3ቱም ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራር ተወካዮች በበኩላቸው የፈጠራ ማዕከላት እንዲነቃቁ እና ተማሪዎቹ ለሌሎቹ አርዓያ እንዲሆኑ ከማስቻል ባለፈ ሠልጣኞቹ ያገኙትን ወደ ተግባር እንዲያውሉት አሳስበዋል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር በለጠ ሞላ በበኩላቸው የፓይለት ፕሮግራም እንደመሆኑ መጠን ወደፊት የተሻለ ሥራ ለመሥራት በር ከፋች መሆኑን ገልጸዋል። በንግግራቸውም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከአጋር አካላት ጋር የተለያዩ ሥራዎችን በመስራት ሐገር በቀል የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እንዲኖሩ የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በመጨረሻም በአውደ ጥናቱ ላይ የበኩላቸውን ለተወጡ አጋር አካላት ዕውቅና የተሰጠ ሲሆን ለሰልጣኞችም የተሳትፎ የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት
ቴሌግራም፡- https://t.me/bitpoly
ዌብሳይት፡- https://bit.bdu.edu.et
Share