የባህር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለጐዳና ተዳዳሪዎች የሙያ ስልጠና ሰጠ

ባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የጐዳና ተዳዳሪ ወጣቶችን ከጐዳና ህይወት ወጥተው ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ የሚያስችል የቴክኒክ ሙያ ሥልጠና በመስጠት አስመረቀ፡፡
ተመራቂዎች በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሜካኒካልና ኢንዱስትሪያል ፋኩልቲ ለ2 ወራት ያህል የተሰጣቸውን መሰረታዊ የብረታብረት ሙያ እና የኢንተርፕረነርሽፕ ስልጠናዎች በተሳካ ሁኔታ ያጠናቀቁ መሆናቸው በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡
ሰልጣኞቹ ባገኙት እውቀትና ችሎታ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ተመልሰው ወደ ጐዳና እንዳይወጡ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ድጋፍ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው በምረቃው ላይ የተገኙ የከተማ አስተዳደሩ ተወካይ ገልፀዋል፡፡
የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ንጉስ ጋብዬ በበኩላቸው ተመራቂዎችን ለማቋቋም በሚደረገው እንቅስቃሴ ኢንስቲትዩቱ ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመቆም እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከከተማ አስተዳደሩ 20 ያክል የጐዳና ተዳዳሪ ወጣቶችን ለማሰልጠን የተረከበ ሲሆን በመጀመሪያ ዙር ስልጠናውን ያጠናቀቁ 9 ሰልጣኞችን ለማስመረቅ መብቃቱ ተገልጿል፡፡
ተመራቂዎች የሰሯቸውን ስራዎች በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ለተገኙ እንግዶች አስጎብኝተዋል፡፡

Share