የብሉ ናይል የውሃ ተቋምና የውሃና  ኢነርጂ ሚኒስቴር  በውሃ፣ ዘውሃ ዲፕሎማሲና ተግባቦት  መድረክ ጉባኤ አካሄደ

መስከረም 06/2015 ዓ/ም፤ [ባዳዩ] የብሉ ናይል የውሃ ተቋምና ኢነርጂ ማዕከል የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ካሉት አምስት የልህቀት ማዕከላት አንዱ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የውሃ ዲፕሎማሲና ተግባቦት መማክርት መድረክ (WHDCF) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበብ አዳራሽ አካሂዷል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ በመገኘት ለተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያቀረቡት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ለተሳታፊዎች በአፍሪካ ከሚገኙ ጤናማና ውብ ከተማ አንዷ ወደ ሆነችዉ እና በዩኒስኮ የትምህርት ከተማ ተብላ ወደተመዘገበችዉ ባሕር ዳር ከተማ እንኳን በሰላም መጣችሁ ብለዋል፡፡

ዶ/ር ፍሬዉ ዩኒቨርሲቲዉ እየሰራቸዉ ካላቸዉ ስራዎች ዋና ዋናዎቹን የገለፁ ሲሆን ከአጋር አካላት ጋር በጋራ በመስራትም ከፍተኛ እምርታ እያሳየ ያለ ዩኒቨርሲቲ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም በአሁኑ ሰዓት ዩኒቨርሲቲዉ ወደ 200 ገደማ ከሚሆኑ አጋር አካላት ጋር በጋራ እየሰራ ሲሆን ይህንንም አጠናክሮ ለመቀጠለል ተግቶ እንደሚንቀሳቀስ አክለዉ ገልፀዋል፡፡ ለዚህም ጠንካራ ተቋማትና ማዕከላትን በመገንባት ላይ መሆኑን ጠቅሰው  የብሉ ናይል የውሃ ተቋምና የኢነርጂ ማዕከል ዩኒቨርሲቲው ካሉት አምስት የልህቀት ማዕከላት አንዱ እና ጠንካራዉ ተቋም ነዉ ብለዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ በመገኘት ለተሳታፊዎች የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ ሀገራት በአንፃራዊነት ሰፊ የሚባል የዉሃ ሀብት ያላት ሀገር መሆኗን ገልፀዋል፡፡ ሀገሪቱ 12 ተፋሰሶች እንዳሏት የገለፁት ሚኒስትር ደኤታዉ ከነዚህ ተፋሰሶች 80℅ የሚሆነዉ የዉሃ ሀብታችን የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠዉ  የሚፈሱና ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የምንጋራቸዉ ተፋሰሶች ናቸዉ ብለዋል፡፡ ድንበር አቋርጠዉ ለሚፈሱ የሀገራችን ዉሃ ሀብቶች ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በሚደረጉ የትብብርና የድርድር ተግባራት ላይ የሀገራችንን ጥቅም ለማስከበር በጥንቃቄ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ አምስት ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበዉ በተሳታፊዎች ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ዉይይቱም በገፅ ለገፅ እና በበይነ መረብ (ኦን ላይን) በቀጥታ ስርጭት የተካሄደ ሲሆን በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የዉሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ የተወካዮች ም/ቤት አባልና የታላቁ ህዳሴ ግድብ አምባሳደር የሆነዉ ሙሀመድ አላሩሲ፣ ታዋቂዉ ተመራማሪና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖን ጨምሮ በርካታ የክብር እንግዶች፣ ምሁራንና የዉሃና የሚዲያ ዘርፍ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

Share